fredag 2. august 2013

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን ሶስት ሕጎችን በማሻሻል ላይ መሆኑ ተሰማ፡፡

በዚህ ሕግ መሠረት የሕዝብ ገንዘብ ዘርፈው ወደውጪ አገር ፈርጥጠዋል የሚባሉ ሰዎች ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል ፡፡
የሚሻሻሉት ሕጎች የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የስነስርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የወጣውን
ረቂቅ አዋጅ፣ የተሻሻለውን የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ
አዋጅ እና የሙስና ወንጀሎችን እንደገና ለመደንገግ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ናቸው፡፡
ረቂቅ አዋጆቹ በኮምሽኑ ተዘጋጅተው የሚመለከተው የመንግስት አካል አስተያየት እንዲሰጥበት የተደረገ ሲሆን በቅርቡ
ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርበው በቀጣይ ዓመት ፓርላማው ያጸድቃቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓርላማ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡
ምንጫችን እንዳብራራው በተለይ የኮምሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ውስጥ የግሉ ዘርፍ በሙስና ወንጀል ለመጠየቅ
የሚያስችለው አንቀጾች ተካተውበታል፡፡
አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ኮምሽኑ የሚመለከተው የሙስና ወንጀል በአመዛኙ የመንግስትን ተቋማት ብቻ የሚመለከት ሆኖ ነገር ግን ወንጀሉ ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር መፈጸሙ ማስረጃ ካለ የግሉን ዘርፍ በተጨማሪነት መክሰስ የሚያስችለው ነው፡፡ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ በተለይ ከሕዝብ በአክስዮን መልክ ገንዘብ ሰብስበው ዞር የሚሉ ሌቦችን ለመቅጣት እንዲያስችለው አክስዮን ማኀበራትን፣ ባንኮችን፣  ኢንሹራንሶችን ፣የልማት ማኀበራትንና የመሳሰሉትን ሕጉ እንዲያቅፍ ተደርጓል፡፡
በግል ባንኮች በተመሳሳይ መንገድ ያለበቂ ዋስትና ብድር የሚሰጥበት፣ ባንኮቹ ከፍተኛ አክስዮን ባላቸው
ግለሰቦችን ተጽዕኖ ስር ሲወድቁና ገንዘባቸው ያለአግባብ በብድር ስም ሲመዘበር ዝም ብሎ ማየት ወይም ተባባሪ
የመሆን ሁኔታ በተደጋጋሚ መከሰቱን፤ በዚህም መንገድ የሕዝብ ገንዘብ ተበልቶ የሚቀርበት ሁኔታ በስፋት በመኖሩ
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሕጉ መሻሻል እጅግ ጠቃሚ ያደርገዋል ተብሎአል፡፡
ይሁን እንጅ ህግ ማውጣት  ብቻውን ሙስናን ለመከላከል በቂ አለመሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ። ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ በገቢዎች ሚ/ር ሰራተኞች ላይ ክስ ከመሰረተ በሁዋላ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አልታየም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar