lørdag 24. august 2013

ከአዲስ አበባ ወደ ወልዲያ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ተገልብጦ በርካታ ሰዎች ሞቱ

ከአዲስ አበባ ወደ ወልድያ ሲጓዝ የነበረ ሚኒባስ አውቶቡስ ደሴ አካባቢ ሲደርስ በመገልበጡ የ21 ሰዎች ህይወት ጠፋ፣ የዛሬውን ጨምሮ በአንድ ሳምንት ውስጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 66 ደርሶአል።
የአደጋው  መንስኤ ጥራት የሌለው የአስፓልት መንገድ በጎርፍ በመቆረጡ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የወልድያ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለኢሳት እንደገለጸው ደግሞ የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ባሙያዎች ከደሴ በመላካቸው መረጃው ተጣርቶ እስከሚቀርብ ድረስ አስተያየት ለመስጠት አይቻልም ብሎአል።
ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ሾፌሩን ጨምሮ የ3 ሰዎች አስከሬን በጎርፍ በመወሰዱ ለማግኘት አልተቻለም። የተወሰኑ አስከሬኖች ወደ ቀወጃ፣ ቆቦ፣ ወልድያና ሳንቃ ተልከው የቀብር ስነስርአታቸው ተፈጽሟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው የሚጥለው ዝናም የአስፓልት መንገዶችን እየጎመደ ጉዳት ማድረሱን  ነዋሪዎች ይናገራሉ። መንገዶቹ የውሀ ፍሳሽ የሌላቸው በመሆኑ በቀላሉ ለአደጋ እንደሚዳረጉ እነዚሁ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ከሁለት ቀናት በፊት በአምባሰል ወረዳ አንድ ሚኒባስ ተሽከርካሪ በጎርፍ በመወሰዷ የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል። በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar