torsdag 8. august 2013

በአዲስአበባ የኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን ዋጋ ጨመረ

በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባልጨመረበት ሁኔታ በአዲስ አበባ ብቻ የኢታኖል ቤንዚን ድብልቅ ነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በ0.16 ሳንቲም ከፍ በማለት በሊትር 18 ብር ከ94 ሳንቲም እንዲሸጥ የንግድ ሚኒስቴር መወሰኑን አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ እንዳመለከተው የዓለም የነዳጅ ዋጋ የመዋዥቅ ሁኔታ ማሳየቱን ተከትሎ ጭማሪ ለማድረግ መገደዱን ይግለጽ እንጂ በዓለም ገበያ በዚህ ወቅት ነዳጅ ዋጋ የተለየ ጭማሪ አለማሳየቱን የዜና ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም በአዲስ አበባ የኢታኖል ቤንዚል ድብልቅ ነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በሊትር ትላንትና ይሸጥበት ከነበረበት ብር 18 ብር 78 ሳንቲም ወደ ብር 18 ብር ከ94 ሳንቲም ከፍ እንዲል የተወሰነ ሲሆን የተቀሩት የነዳጅ ምርቶች ማለትም ነጭና ጥቁር ናፍታ፣አብዛኛው ህብረተሰብ ለማገዶ የሚጠቀምበት ኬሮሲን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ በሐምሌ ወር በሥራ ላይ የነበረው ዋጋ በያዝነው ነሐሴ ወርም በተመሳሳይ እንዲቀጥል ወስኖአል፡፡
በዓለም ገበያ ላይ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ ሁኔታ መነሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ከነሐሴ ወር በኃላም ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችልም ሚኒስቴሩ ገልጾአል፡፡
ሚኒስቴሩ በየወሩ የሚያደርገው የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ተከትሎ የትራንስፖርት ክፍያ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ የመጣ ሲሆን ይህም የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሲሆን ቆይቷል፡፡ በአዲስአበባ በአሁኑ ወቅት የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ ከ5-9 ብር የሚሸጥበት ዋናው ምክንያት ከነዳጅ ጭማሪ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ በሚቀንስበት ወቅትም የጨመሩት የሸቀጥ ዋጋዎች ባሉበት መቀጠላቸው የሚታወቅ መሆኑን ዘጋቢያችን ከአዲስአበባ የላከው ዜና ጠቁሟል

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar