søndag 3. februar 2013

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ



ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ በትናንትናው እለት በደህንነት ሀይሎች ታፍነው የተወሰዱት 2ቱ ጓደኞቻቸው የት እንዳሉ ዩኒቨርስቲው እንዲያሳውቃቸው ጠይቀዋል።

የዩኒቨርስቲው አስተዳዳሪዎች ከተማሪዎች ለቀረበው ጥያቄ ” ተማሪዎቹ በደህንነት ሀይሎች ተፈልገው የተወሰዱ በመሆኑ እኛ ምንም ማድረግ አንችልንም፣ ለወደፊቱም የፍርድ ቤት ማዘዣ ይዘው ከመጡ አሳልፈን እንሰጣለን” በማለት መልስ መስጠታቸው ታውቋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች እንደገለጡት በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ እየጨመረ በመምጣቱ ትምህርታቸውን ተረጋግተው ለመማር አልቻሉም።

በደህንነት ሀይሎች የተወሰዱት ሰይድ እና ኡመር የተባሉት ተማሪዎች በዚህ አመት ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር። በሙስሊም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በተመሳሳይ ዜና በሐረር ኢማን መስጂድ ዘበኛ የነበሩት ስማቸው ለጊዜው ያልታወቀው ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ታውቋል።

 ግለሰቡ ከመገደላቸው በፊት በአካባቢው መብራት ጠፍቶ የነበረ ሲሆን፣ ሁኔታው ከተረጋጋ በሁዋላ መብራት ተመልሶ መምጣቱ ታውቋል።

መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን የሰጠው መልስ የለም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar