tirsdag 26. februar 2013

በብራሰልስ የኢሳት የገቢ ማሰባሰብ ዘግጅት ተካሄደ



እውቁ አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ በተገኘበት ትናንት የካቲት 17፣2005 ዓም የተካሄደው የኢሳት የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት በቤልጂየም የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።

ከሰአት በሁዋላ የተጀመረው ስብሰባ የተከፈተው በቤልጂየም የኢሳት የገቢ አሰባሳቢ ግብረሀይል ወኪል በሆኑት በአቶ ገበየሁ ደስታ ነበር። በመቀጠልም ሌላው የኮሚቴ አባል አቶ ኤፍሬም ሻውል ኢሳት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠውን ግልጋሎት የተመለከተ ጥናታዊ ወረቀት አቅርበዋል።

 አቶ ኤፍሪም እንደገለጡት ኢሳት መረጃ ከመስጠት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ሙስና ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና የመልካም አስተዳደር እጦት ከማጋለጥ ባሻገር የኢትዮጵያውያን የትግል መንፈስ የማነቃቃት ሚና እየተጫወተ ነው።

ከአቶ ኤፍሪም በሁዋላ ንግግራቸውን ያቀረቡት የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል እና በኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የያዙት የተከበሩ ሚስ አና ማርያ ጎሜዝ ተወካይ ናቸው።

 ክብርት አና ጎሜስ በጽሁፍ ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚፈጽማቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ከገለጹ በሁዋላ ተቃዋሚዎች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው በአንድነት በመቆም፣ ለውጥ እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 ሚስ አና ጎሜዝ ተቃዋሚዎች በህብረት ከታገሉ ገዢውን ሀይል በማስወገድ ሁላችንም መስቀል አደባባይ ላይ ተገናኝተን ድላችንን የምናከብርበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም ብለዋል።

ሌላው ተናጋሪ በቤልጂየም የሉቅማን ኢትዮጵያውያን ቤልጂየማውያን ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አብየ ያሲን ሲሆኑ፣ አቶ አብየ በአሁኑ ጊዜ በምርጫ 97 ወቅት ባልተናነሰ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በፊዲዮ አስደግፈው አቅርበዋል።

በእለቱ የብዙዎችን ስሜት የነካ ንግግር ካቀረቡት ተናጋሪዎች መካከል የአፋር ህዝብ ፎረም ሊቀመንብር አቶ ጋአስ አህመድ አንዱ ነበሩ። ” አቦይ ስብሀት አፋርን ኢትዮጵያዊነቱን ያስተዋወቅነው እኛ ነን” በማለት የተናገሩትን ያወሱት አቶ ገአስ፣ “ኢትዮጵያን የሰው ልጅ መገኛ አገር ያስባለቻት ሉሲ የተገኘችው ከአፋር ምድር ነው፣ እንዴት ነው ታዲያ አቶ ስብሀት ለአፋር ኢትዮጵያዊነቱን ያስተዋወቁት?” በማለት ጠይቀዋል።

' እንዲሁም ” አፋሮችን ከሽርጥ አውጥተን ሱፍ ያለበስናቸው እኛ ነን ይሉናል ያሉት አቶ ገአስ፣ “ለእኔ ግን ሱፉ ቀርቶብኝ ነጻነቴን ሰጥተውኝ በሽርጤ ብኖር ይሻለኛል።

” በማለት በአፋር ክልል እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዘርዝረዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት አርቲስቲትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ የቤልጂየም የኢሳት ኪሚኒቲ ባዘጋጀለት ሊሞዘን ወደ አዳራሹ ሲመጣ፣ የአፋር ወጣቶች ጊሌያቸውን በመያዝ ውብ በሆነ ባህላዊ ጭፈራ ተቀብለውታል።


 ወጣቶቹ አርቲስቱን አጅበው ወደ አደራሹ ከገቡ በሁዋላ የተለያዩ የአፍርኛ ሙዚቃዎችን ለተመልካቹ ተጫውተዋል።

አርቲስት ታማኝ የተመልካቹን ስሜት ሙሉ በሙሉ በገዛበት ንግግሩ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ፍርተው ተሰደው፣ በውጭ አገርም በፍርሀት እንደሚኖሩ፣ ፍርሀቱም እየደረሰብን ላለው መከራ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግሯል ።


በእለቱ ከጫረታ ከ5 ሺ ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ተሰብስቧል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar