onsdag 27. februar 2013

የሳውዲው ም/ል የመከላከያ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ወቀሱ


ምክትል የመከላከያ ሚኒሰትሩ ካሊድ ቢን ሱልጣንን በመጥቀስ ሱዳን ትሪቢዩን እንደዘገበው፣ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ምትገነባው ፕሮጀክት ለሱዳንና ግብጽ ከፍተኛ አደጋ አለው በማለት ተናግረዋል።

ግድቡ በ700 ሜትር ከፍታ ላይ የሚሰራ በመሆኑና 70 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ የሚይዝ በመሆኑ፣ ግደቡ ቢፈርስ ሱዳን ሙሉ በሙሉ ስትሰምጥ፣ የግብጽ አስዋን ግድብ ደግሞ አደጋ ያጋጥመዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ግብጽ ሌላ አማራጭ ውሀ የሌላት በመሆኑ ከሁሉም በላይ እንደምትጎዳ የገለጡት ሚ/ር ካሊድ፣ ግድቡን ከሱዳን ድንበር 12 ኪሎሜትር እርቀት ላይ ለመስራት የተፈለገው ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ ይልቅ የፖለቲካ ሴራ ለማሴር ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአረብ አገራትን ለመጉዳት ሆን ብላ የነደፈችው ፕሮጅክት ነው ብለዋል። ግድቡ ከፍተኛ የሆነ ውሀ የሚሸከም በመሆኑም በአካባቢው ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያስከትል ይችላል።

የሳውዲው ወኪል ግብጽን በመወከል እንዲናገሩ ያስገደዳቸው ምክንያት በውል አልታወቀም። የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳንና ግብጽ ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ሲገልጽ ቆይቷል።

 ሟቹ ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊ ከአንዳንድ አፈንጋጭ ግብጻዊያን በስተቀር አብዛኛው ግብጻዊ በአባይ ላይ በሚሰራ ፕሮጀክት ተቃውሞ እንደሌለው ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

የግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ሄደው በነበረበት ወቅትም፣ ግብጽ በአገሪቱ የተነሳው አብዮት ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንደምትፈልግ መጠየቋ በኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ብዙሀን ቀርቦ ነበር።

የሳውዲው ሚኒስትር ንግግር ግብጽ በአባይ ላይ የሚሰራውን ግድብ አጥብቃ እንደምትቃወም የሚያመላክት ነው።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar